Wednesday, July 20, 2011

ገጣሚ በዕውቀቱ ሥዩምና የእግር ኳሳችን አቤቱታ! Bewketu Seyoum Poem

እጇ ላይ ነጣ ያለ መፅሐፍ ይታያል፡፡ አንድ ቅዳሜ ቀን ነው፡፡ መፅሐፏን እያሻሸች "ሁሌም የማንገናኘው ግን ለምንድን ነው?" አለችኝ፡፡ ብዙ ጊዜ አንስታብኝ የተለያየ መልስ ስለሠጠኋት አሁን ምንም አላልኳትም፡፡ በቀጠሯችን የማልገኝበትን ምክንያት መዘክዘክ ሰልችቶኛል፡፡ ስለዚህም understand እንድታደርገኝ ብዬ ስታዲየም ይዣት ገባሁ፡፡ ኳሱን እያየን ሳለ ሠረቅ አድርጌ አየኋት፡፡ አንገቷን አቅንታ ወደ ሰማይ እያየች ቢሆንም የምታየው ግን ሰማዩን አልነበረም፤ የማይታይ ነገር ነበር እያየች የነበረችው! የማይታይ ሲባል ደግሞ ለእርሷ ብቻ የሚታይ የተለየ ነገር ኖሮ አልነበረም፡፡ ይልቁኑ አንዱ ከአፍሪካ ሃገር በፕሮፌሽናልነት ወደ ቡና ክለብ የመጣ በረኛ ወደ ሰማይ ያጎናትን ኳስ በዓይኗ እየተከተለች ነበር፡፡ ኳሷ እንደምንም ብላ ወደ መሬት ብትወርድም የእሷ ዓይኖች ግን አብረዋት አልወረዱም፡፡ ብዙም ሳይቆይ ዳኛው የዕረፍት ፊሽካ ነፍተው ጨዋታው ቆመ፡፡ የእሷ ዓይኖች ግን እዚያው ደመናማው ሰማይ ላይ ተተክለው ቀርተዋል፡፡ ምናልባት በዚያው ስለ ፉትቦላችን ትንሽዬ ፀሎት ነገር ማድረግ ሳያምራት አልቀረም፡፡በድንገት ግን ምን እንደተገለጠላት እንጃ ወደ እኔ ዘወር አለችና "ከዕረፍት እስቲገቡ ትንሽ ግጥም ላንብብልህ?" ብላኝ መፅሐፏን ገለጥ ገለጥ አድርጋ አንድ ግጥም አነበበችልኝ፡፡ ግጥሙ በጣም ከየፈኝ፡፡ በቁንፅሉ እንዲህ ይላል፡፡

". . .

ጥንቸሉ ሐሳቤ ‑ ንሥሩ የቀን ሕልሜከዔሊው ቅልጥሜ ‑ ከጫጩቱ አቅሜያላቻ ተጋጥመው ሰርክ ሲፎካከሩያለመዳረሻ ‑ ያለፅኑ ወደብ ‑ ሲያባዝኑኝ ኖሩ. . ."

መፅሐፉ 'ስብስብ ግጥሞች' የተባለው የበዕውቀቱ ሥዩም መፅሐፍ ሲሆን በገፅ 50 ላይ የፃፈውን ግጥም ነበር ያነበበችልኝ፡፡መቼም 'ሳይንሳዊ አሠለጣጠንን እንከተላለን' ለሚሉት ላገራችን 'ምኁር' አሠልጣኞች ይህችን የመሠለች ግጥም ለማብራራት መሞከር ማለት እነሱን ብቻ ሳይሆን ገጣሚውንም መናቅ፤ የግጥሙንም ደረጃ ዝቅ ማድረግ ነው የሚሆነው፡፡ አሠልጣኞች እስቲ እባካችሁ እንደገና ግጥሟን አንብቧት፡፡በዕውቀቱ ሥዩም ግጥሟን 'ዕረፍቴን አሥሣለሁ' ብሎ ሠይሟታል፡፡ እግር ኳሳችንም የሚጫወተው እና የሚያሣርፈው አጥቶ 'ሐሠሣ ዕረፍት' ላይ ነው፡፡ ቡድኖቻችንን በዓለምአቀፋዊ ውድድሮች ላይ ባለድል የማድረግ ምኞት ያላቸው አሠልጣኞች ያሉባት ሃገር ብቻ አይደለችም ‑ ኢትዮጵያ፡፡ ነገር ግን የእግር ኳስ ተጫዋቾቿም በተፈጥሯቸው አናሳና፣ ደቃቃ የሆኑባት ሃገር ናት፡፡ እግር ኳሳችን እነዚህ ሁለት የተለያዩ ነገሮቸን (ምኞትና አቅም) ማመጣጠን ባልቻሉ ወይም እንደ ግጥሙ በግድ ባፎካከሩ አሠልጣኞቻችን የተነሣ 'ሐሠሣ ዕረፍት' ላይ ነው፡፡የአሠልጣኞች ሕልም ብቻ የሚያስተዳድረው አሠለጣጠን በአንደኛው ዋልታ ላይ ይገኛል፤ የተጫዋቾቻችን ተፈጥሯዊ ማንነትና አቅም ደግሞ በሌላኛው ዋልታ ላይ ነው ያለው፡፡ እነኚህ ሁለት የተለያዩ ነገሮች በሁለት የተለያዩ ፅንፎች ላይ በተገኙበት ሁኔታ እግር ኳሳችን ልክ መሐል ውቅያኖስ ላይ ሳለች አቅጣጫዋ /ኮምፓሷ/ እንደጠፋባት መርከብ ሆኖ እየባዘነ ነው፡፡ ለዚህም ኃላፊቱን መውሰድ የሚገባቸው ራሳቸው አሠልጣኞቻችን ናቸው፤ ምክንያቱም የሚከተሉት ታክቲክና ሥልጠና ተጫዋቾቻችን ያላቸውን ክህሎትና የሌላቸውን ጉልበት ያላገናዘበ ስለሆነ ነው፡፡ይህን ስል ታዲያ መላው ኳስ አፍቃሪ ስታዲየም ገብቶ ሊያደንቃቸውና ሊያበረታታቸው የሚገባቸው ምርጥ ምርጥ ተጫዋቾቻችንን ሳልዘነጋ ነው፡፡ ካሠልጣኞቹ ታክቲከ አፈንግጠው ክህሎታቸውን የሚያሳዩን ዕፁብ ድንቅ ተጫዋቾች አሉን፡፡ ለምሳሌ የኤልፓው ሳሚ ከደደቢት ጋር ያሳየንን ድሪብሎች እንዴት አሪፎች እንደነበሩ ማን ይዘነጋል? የጊዮርጊሱ ሚኬሌስ መተሐራ ላይ የሠራቸውን አብዶዎች ማን ነው የማያደንቅ? የዳዊት እስጢፋኖስ ጓደኞቹን ለመርዳት ሁሉም ቦታ መገኘትስ? የትኛው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋች እንደዚህ ያደርጋል? ሰብስቤ ሸገሬ ቴክኒሺያንነቱን ትተን አዳማ ከነማ ላይ ያገባትን ኳስ ማን ይረሳል? ከተጫዋቾቹ የግል ክህሎት በስተቀር በ2002 ብቻ ከታዳጊ ቡድኑ ጀምሮ ባንክን ጨምሮ እስከ ጊዮርጊስ ድረስ ከድሮ እስከ ዘንድሮ እየተከተሉት ባሉት ተመሳሳይ ታክቲክ ተበልጠው ከኢንተርናሽናል ውድድር ወጥተዋል፡፡እስቲ ለማንኛውም ወደ ጉዳያችን እንመለስ፡፡ ከላይ በግጥሙ ላይ እንዳስተዋልነው ፍላጎትና አቅም አልመጣጠን ካሉ እኮ አበሳ ነው፤ አንድም ፍላጎትን መገደብ ወይም ደግሞ አቅምን መጨመር ያሻል፡፡ 1ኛ ፍላጎትና ምኞትን መገደብ ማለት ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አለመሳተፍ፣ ከዓለም ዋንጫ ማጣሪያም በፈቃደኝነት መውጣት፣ ለአፍሪካ ክለቦችም ሆነ ለካፍ ካፕ ውድድሮች አለመጫወትና ያገር ውስጥ ሊጉን መዝጋት ማለት ሲሆን ይህ ደግሞ በአጠቃላይ በፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡2ኛ አቅምን ማሳደግ የሚለውን ስናየው ደግሞ በተናጠል ለሚተገበረው የእግር ኳስ ታክቲክ የሚጠቅም ፊዚካል እንዲኖራቸው ተጫዋቾቻችንን ጉልበትና ፍጥነታቸውን ማሳደግ ማለት ነው፡፡ ይህም አያስኬድም፡፡ የማያስኬደው ስለማይቻል ነው፡፡ ምክንያቱም የተጫዋቾቻችን አካላዊ ተፈጥሮ ለውጥ ቢያመጣና ቢደረጅ እንኳ በፍፁም እንደሚታሠበው ከአፍሪካዊያኑ ጋር ሊነፃፀር የሚችል አይሆንም፡፡ ማን ነበረ የኬንያዋ ቆንጆ እዚህ እኛ ሀገር መጥታ "ፀጉሯ ወርዶ ወርዶ ከጆሮዋ በላይ ነው" ያላት? የኛም ተጫዋቾች የፊዚካል ጥንካሬም ሆነ የፍጥነት ለውጥ ቢያመጡም ኢምንት ነው፤ እሱም እዚሁ ለእርስበርስ ንፅፅር እንጂ ለሌላ ለምንም አይፈይድም፡፡ ክቡር ጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ አንድ ጊዜ እንደተናገሩት እኮ 80 ኪሎ የሚመዝን ቦክሰኛ እንኳን ማፍራት አልቻልንም፡፡ (ሊያውም እሳቸው ይህን ያሉት ከ20 ዓመታት በፊት ነው፡፡) ስለዚህ አካላዊ ዕድገት ለማምጣት የምንሠራው ሥራ ከአፍሪካዊያኑ ጋር በጭራሽ አያስተካክለንም ማለት ነው፡፡ ያ ማለት ደግሞ አካል ብቃት ላይ (intensively) መሥራት ሊያመጣ የሚችለው ምንም እግር ኳሳዊ ለውጥ የለም ማለት ነው፡፡ምኞትና ፍላጎት (ማለትም የአፍሪካን ዋንጫ የማግኘትንም ሆነ የመሳተፍ) አልገደብ ካለ፣ የተጫዋቾቻን አቅምም አላድግ ካለ እንግዲህ ወደ ሦስተኛውና ብቸኛው አማራጭ ከመሔድ ውጭ ምን አማራጭ አለን? ይህም 'ብልኃትን መጠቀም' የሚል ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡ ይህ አማራጭ ፍላጎታችንን ሳንገድብ፤ ከንቱ አካላዊ ልፋት ውስጥም ሳንገባ ያለንን ብልኃት ተጠቅመን ባለችን አቅምና ተክለሰውነት ያልተገደበውን ፍላጎታችንን እንድናሳካ የሚረዳን ትክክለኛ አማራጭ ነው፡፡

"ይህ ብልኃት ምንድን ነው?" ከተባለ እሱን ለመግለፅ በርካታ ኢትዮጵያዊ አባባሎችን ልናነሳ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ሰሚ ጆሮ ላለው፣ አስተዋይ አዕምሮ ለታደለ አሠልጣኝ እነዚህ ሁለት አባባሎች ብቻ ስለሚበቁት ብዙ ዝርዝር ነገሮችን አንስተን መዘብዘብ አያስፈልገንም፡፡ ላንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ! ወይም ድር ቢያብር አንበሳ ያስር! በቃ! ተረዳድተን የምንጫወትበትን በ1995 ካሳዬ አራጌ ሜዳ ላይ ያሳየንን ታክቲክ መተግበር አለብን! በዚህ ሁኔታ ለሃገራችን ተጫዋቾች ወደሚያዋጣ፤ ለእግር ኳሳችንም መፍትሔ ወደሆነ ትክክለኛ አሠለጣጠን ማምራት ግድ ይላል፡፡ አለዚያ ግን እንደእስተዛሬው ሁሉ መባዘንና ዕረፍት ማጣት ውስጥ ነው ፉትቦላችን የሚዳክረው፡፡በነገራችን ላይ ጓደኛዬ የእስታሁኑን የስታዲየም ቆይታችንን ወዳዋለች፡፡ አሪፍ ቴክኒካል ክህሎቶችንም አይታለች፡፡ አውሮፓ ውስጥ አሉ የሚባሉ ጎሎችን እዚህ አዲስ አበባ ስታዲየም እነ ሰብስቤ ሸገሬ እንደዘበት ሲያስቆጥሩ አይታ ረክታለች፡፡ ግን በተለጋችው ኳስና ከኢንተርናሽናል ውድድሮች 3ቱም የኢትዮጵያ ቡድኖች ተሸንፈው መውጣታቸውን ስነግራት ትንሽ አዝና ስለነበረ ነው ግጥሙን በጨዋታው የዕረፍት ሰዓት ላይ ያነበበችልኝ፡፡ያም ሆነ ይህ በዕውቀቱ የግጥሙን መታሰቢያነት ለአሠልጣኞቻችንና ለታክቲካቸው ባያደርገውም፤ ጓደኛዬ ግን አንዲት የበፊት ሙዚቃ ልትጋብዛቸው ፈለገች፡፡

".

. . አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነውታላቅ ችሎታ ነው . . ."

ደግሞ እናንተ ሰዎች (ማለት አሠልጣኞች) እባካችሁ ዘፈኑን አጣጥማችሁ መስማት ብቻ ሳይሆን የታክቲካችሁ ፍልስፍናም መሠረት አድርጉት፡፡ የተጫዋቾቻችንን ክህሎት ለይታችሁ አወቃችሁ ማለት እኮ አቅማችሁን አወቃችሁ ማለት ነው ‑ ይህ ደግሞ ታላቅ ችሎታ ነው፡፡ ክህሎት ያላቸውን ኢትዮጵያዊ ተጫዋቾችን የምትጠቀሙበትን ተስማሚውን ታክቲክ ከተገበራችሁ ደግሞ ታላቅ ብልኅነት ነው፡፡ ያን ጊዜ ነው እስተዛሬ ድረስ የማንጋፋቸው ባላጋራ የሆኑብንን አፍሪካዊያን በእግር ኳስ ውስጥ የማያውቁት ዓለም እንዳለ የምናስረዳቸው፡፡ አለዚያ ታውቁታላችሁ አይደል? 'እግር ኳስ ውጤት ነው' በማለት ብቻ በናንተ ዓይነቱ የእግር ኳስ ታክቲክና ሥልጠና እንኳንስ ውጤትና ዋንጫ ልታመጡ ወደ ስታዲየም እየተመለሠ ያለውንም ኳስ አፍቃሪ ታስኮበልላላችሁ፤ የናንተን ዓይነት የሻሞ አጨዋወትም ከማንም በተሻለ የሚጫወቱ፤ እቤቱ ድረስ እየመጡ በቲቪ የሚያያቸው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾችም እስታፍንጫው ድረስ ነፍ ናቸው፡፡

አሠልጣኞች ሆይ እባካችሁ ለእግር ኳሳችን እሰቡለት!አንድዬ እሱው አቅማችሁን ያሳውቃችሁ! ልካችሁን ይንገራችሁ!ዳዊት ከአዲስ አበባ

1 comment: