Thursday, March 22, 2012

የፊታችን ቅዳሜና እሁድ

ፊታችን ቅዳሜና እሁድ አንድ ታላቅ ድግስ በአዲስ አባባ ስታዲየም ተደግሷል.. በዚህ በፆም ሰንጋ ታርዶ እንደጉድ የሚበላ እንዳይመስልህ፡፡ የደስታ ይሁን የሀዘን ዉሉ የማይታወቅና ሊገመትም የማይችል ድግስ፡፡ አዎ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጲያ ቡና ኢንተርናሽናል ጨዋታቸዉን ያደርጋሉ፡፤ ከምንም በላይ አዲስ አበባ ስታዲየም መገኘት ከሚያስደስተዉ ሰዎችመሀከል አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ደግሞ ምን አለና እንዳትሉኝ.. ገና በጠዋቱ በፀሀይና በሙቀቱ እየተጠበሰ የ5ና የ10 ብር ቲኬት ለማግኝት የሚጋፋዉን አልያም ዉበት ለሌለዉ ጨዋታ 50 ና 100 ብር ከፍሎ ጥላ ፎቅ የሚገባዉን ስፖርት አፍቃሪ ጠይቁት፡፡ እዉነት እላችኋለሁ ከጨዋታዉ ይልቅ ሜዳዉ ዉስጥ ባለዉ ድባብ ልባችሁ ሀሴት ታደርጋለች.. እናንተ ብቻ የስፖርት አፍቃሪ መሆን አይጠበቅባችሁም፡፡ በእለቱ ስራ ከሌለብህ አልያም የምትሄድበት ብታጣ ወደ ስታዲየም ለመምጣት አታቅማማ፡፡ እዉነተኛ የክለቦቹ ደጋፊ ከሆንክ ፈንጥዘህ አልያም ተቃጥለህ ልትወጣ ትችላለህ፡፡ የማንም ክለብ ደጋፊ ካልሆንክ ግን ተገርመህ ልትወጣ ትችላለህ፡፡ ቢቻል የፊታችን ቅዳሜና እሁድ ብቅ በል .. በስፖርቱ ያበደዉ አፍቃሪ አንድ ድምፅ ክለቦቹን ሲደግፍ ታያለህ፡፡ በዚህ ቀን መምጣት ካልቻልክ ግን ቡናና ጊዮርጊስ ሲጫወቱ ጠብቀህ ጎራ በል..ያኔ እርስ በርሳቸዉ የቃላት መትረየስ ሲለዋወጡ ታያለህ፡፡ በዚህም ቀን መምጣት የማትችል ከሆነ ግን መቼም አትምጣ፡፡ ምክንያቱም ከነዚህ ጨዋታዎች ዉጭ ስታዲየሙ ባዶ ነዉና፡፡ ብቸኝነት ካማረህ ግን ሌሎች ክለቦች ሲጫወቱ ብቅ በል.. ያኔ መነሻቸዉን አምባሳደር መድረሻቸዉን ደግሞ ስታዲየም ካደረጉ ብዛት ካላቸዉ አሞራዎች ጋር ሆነክ ዘና ብለህ ማየት ትችላለህ.. ያዉ ከተግባባሀቸዉ ከነሱ ጋር ሆነህ መዘመር ነዉ፡፡ ስታዲየም ገብተህ የማታዉቅ ጓደኛዬ ሆይ! ቅዳሜና እሁድ ቀጠሮህን ስታዲየም ይሁን፡፡ ትኬት ለማግኘት ግርግሩ የሚያስጠላህ ከሆነ እኔን ጠይቀኝ.. ላንተ ስል ተጋፍቼ በመቁረኝ ይህን ልዩ ትርኢት ታይ ዘንድ ልረዳህ ቃል እገባልሀልሁ፡፡ ምንም እንኳን የጊዮርጊስ ደጋፊ ብሆንም የኢትዮጲያ ቡና ተጋጣሚ የሆነዉ የግብፁ አል አሊ ስኳር የሌለበት መራራ ቡና ጠጥቶ ወደ ሀገሩ ይመለስ ዘንድ የበኩሌን ድጋፍ ለመስጠትና ቡና ገበያ አደገኛ ለማለት ለቡና ደጋፊዎች ቃል ገብቻለሁ፡፡ መልካም እድል!!!

No comments:

Post a Comment